ረቡዕ 1 ጁላይ 2015
ክፍል አንድ ምስጢረ ሥላሴ የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ምስጢር ምስጢር የሚለው ቃል አመሰጠረ፣ ሰወረ፣ አረቀቀ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ፍቺውም ረቂቅ፣ ስውር፣ ኅቡዕ ማለት ነው፡፡ ምስጢር መባሉም የሥላሴን ባሕርይ ፍጡር መርምሮ የማይደርስበት በመሆኑ፣ በፍጡር ባሕርይ መወሰን፣ መጨረሻውን ማወቅ የማይቻልና ከፍጡር እውቀት አቅም በላይ በመሆኑ ነው፡፡ ሥላሴ የሚለው ቃል ደግሞ ሠለሰ ሦስት አደረገ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሦስትነት ማለት ነው፡፡ቅድስት ሥላሴ: - ለሥላሴ ቅድስት ብለን እንቀጽላለን፡፡ ቅድስት ሥላሴ ማለት ልዩ ሦስትነት ማለት ነው፡፡ ይህም ሦስት ሲሆን አንድ፣ አንድ ሲሆኑ ሦስት ስለሚሆኑ ልዩ ሦስትነት ተብሏል፡፡ ስለዚህ ነገር መጽሐፈ ቅዳሴያችን ሥላሴ ሦስት ናቸው ስንል እንደ አብርሃም እንደ ይስሐቅ እንደ ያዕቆብ ማለታችን አይደለም ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸው እንጂ፣ አንድ ናቸውም ስንል ቀዳሚ ሆኖ እንደተፈጠረው እንደ አዳም ማለታችን አይደለም አንድ ሲሆኑ ሦስት ናቸው እንጂ፡፡ /ቅዳሴ ማርያም/፡፡ ቅድስት ተብሎ በሴት አንቀጽ መጠራቱ ደግሞ እናት ለልጇ ስለምታዝንና ስለምትራራ ሥላሴም ለፍጥረታቸው ምሕረታቸው ዘለዓለማዊ ነውና ቅድስት ይባላሉ፡፡ በዚህ መሠረት ምሥጢረ ሥላሴ ማለት የአንድነት የሦስትነት ምስጢር ማለት ነው፡፡ ይኸውም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስት ሲሆኑ በባሕርይ በሕልውና፣ በመለኮት ደግሞ አንድ ናቸው፡፡ እንደዚህ ባለ ድንቅ ነገር አንድ ሲሆኑ ሦስት፣ ሦስት ሲሆኑ አንድ ይባላሉና፣ ይህም ልዩ ሦስትነት ረቂቅ እና በሰው አእምሮ የማይመረመር ስለሆነ ምስጢር ይባላል፡፡ የሰው ልጅ ሁሉን የመመርመርና የመረዳት መብትና ሥልጣን ከአምላኩ የተሰጠው መሆኑ ቢታወቅም የፈጣሪን ባሕርይና ጠባዮቹን ለመገንዘብ ውሱን ከሆነው አቅሙ በላይ ስለሚሆንበት በእምነት ከመቀበል በቀር ሌላ አማራጭ መንገድ ሊኖረውም አይችልም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት በማድረግና ከቅዱሳን አባቶች በተላለፈልን ትምህርት መሠረት ኃያሉ እግዚአብሔርን በአንድነትና በሦስትነት እናምነዋለን፡፡ እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስት፣ ሦስት ሲሆን አንድ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ የእግዚአብሔርን አንድነት የምናምነው፡- በፈጣሪነት፣ በአምላክነት፣ በአገዛዝ፣ በፈቃድ፣ በሥልጣን እነዚህን በመሳሰሉት የመለኮት ባሕርያት ነው፡ /መለኮት ወይም ማለኹት/ በዕብራይስጥ ቋንቋ መንግሥት ማለት ነው፡፡ በግዕዝ ግን ባሕርይ፣ አገዛዝ፣ ሥልጣን ማለት ነው፡፡ ሦስትነቱን የምናምነው ደግሞ በስም፣ በግብር /በኩነት/ በአካል ነው፡፡ «እንዘ አሐዱ ሠለስቱ ወእንዘ ሠለስቱ አሐዱ፣ ይሤለሱ በአካላት ወይትዋሐዱ በመለኮት» እንዳለ /ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ/፡፡ ሀ/እግዚአብሔርበአንድነቱየሚታወቅበትስሞች1. ፈጣሪ 2. አምላክ 3. ጌታ 4. መለኮት 5. እግዚአብሔር 6. ጸባኦት 7. አዶናይ 8. ኤልሻዳይ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ለ/እግዚአብሔርበሦስትነቱየሚታወቅባቸውስሞችደግሞ 1. አብ 2. ወልድ 3.መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ ሐ/እግዚአብሔርበግብርሦስትነቱየሚታወቀው 1. አብ ወላዲ፣ አሥራፂ በመባል፣ 2. ወልድ ተወላዲ በመባል፣ 3. መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ በመባል ነው፡፡ የአብ ግብሩ መውለድ፣ ማስረጽ ሲሆን የወልድ ግብሩ መወለድ፣ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መስረጽ ነው፡፡ አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ /የወጣ፣ የተገኘ/ ነው፡፡ አብ አባት ነው፣ ወልድ ልጅ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ የሠረፀ ነው፡፡ /ዮሐ.14-26/፡፡ ሦስቱ አካላት አንድ መለኮት ናቸው፡፡ ሠለስቱ ስም አሐዱ እግዚአብሔር እንዳለ /አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው/፡፡ የአካል ሦስትነታቸውም ለአብ ፍጹም አካል፣ ፍጹም መልክ፣ ፍጹም ገጽ አለው፤ ለወልድም ፍጹም አካል፣ ፍጹም መልክ፣ ፍጹም ገጽ አለው፤ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል፣ ፍጹም መልክ፣ ፍጹም ገጽ አለው፡፡ እንዲህ ሲባል ግን የሥላሴ አካል አንደ ሰው አካል ውሱን፣ ግዙፍ፣ ጠባብ አይደለም፡፡ ምሉዕ፣ ስፉሕ፣ ረቂቅ ነው እንጂ፡፡ ምሉዕነታቸውና ስፋታቸው እንዴት ነው? ቢሉ ከአርያም በላይ ቁመቱ፣ ከበርባኖስ በታች መሠረቱ፣ ከአድማስ እስከ አድማስ ስፋቱ ተብሎ አይነገርም፣ አይመረመርም፡፡ ምክንያቱም ሥላሴ ዓለሙን ይወስኑታል እንጂ ዓለሙ ሥላሴን አይወስናቸውምና፡፡ ርቀታቸውስ እንዴት ነው? ቢሉ ከሁሉ ነፋስ ይረቃል፡፡ ከነፋስ መላእክት ይረቃሉ፡፡ ከነፍሳትና ከመላእክት ደግሞ ኅሊናቸው ይረቃል፡፡ ይህ የኅሊናቸው ርቀት በሥላሴ ዘንድ እንደ አምባ እንደ ተራራ ነው፡፡ በዚህም ርቀታቸው በፍጥረት ሁሉ ምሉዓን፣ ኅዱራን ናቸው፡፡ ባሕርያቸውም የማይራብ፣ የማይጠማ፣ የማይደክም፣ የማይታመም፣ የማይሞት ሕያው ነው፡፡ «ስምከ ሕያው ዘኢይመውት ትጉህ ዘኢይዴቅስ ፈጣሪ ዘኢይደክም» እንዳለ /ቅዲስ ባስልዮስ በማክሰኞ ሊጦን/፡፡ መ/የኩነት /የሁኔታ/ሦስትነት ኩነት በህልውና /በአኗኗር/ እያገናዘቡ በአንድ መለኮት የነበሩ፣ ያሉ፣ የሚኖሩ ናቸው፡፡ እነርሱም፡- 1. ልብነት፡- በአብ መሠረትነት ለራሱ ለባዊ /አዋቂ/ ሆኖ ለወልድ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ልብ፣ ዕውቀት መሆን ነው፡፡ 2. ቃልነት፡- በአብ መሠረትነት ለራሱ ነባቢ /ቃል/ ሆኖ ለአብ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ቃል መሆን ነው፡፡ 3. እስትንፋስነት፡- በአብ መሠረትነት ለራሱ ሕያው ሆኖ ለአብ፣ ለወልድ ሕይወት መሆን ነው፡፡ ስለዚህ በአብ ልብነት ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸው ያስቡበታል፤ በወልድ ቃልነት አብ፣ መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸው ይናገሩበታል፤ በመንፈስ ቅዱስ አስትንፋስነት አብ፣ ወልድ ህልዋን ናቸው ሕያዋን ሆነው ይኖሩበታል፡፡ ታላቁ ሐዋርያ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ 1ዐ-17 ላይ «እምነት ከመስማት ነው፣ መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል ነው» ብሎ እንደተናገረው ከላይ የተጠቀሱትን መጠነኛ ማስረጃዎች በሙሉ ለመገንዘብ እንዲቻል የእግዚአብሔር እስትንፋስ የሆኑትን የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎችን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ሥላሴ የሚለው ስም እንዲያው የመጣ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በአንድነቱና በሦስትነቱ የሚጠራበት የከበረና ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም ነው፡፡ ለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ /ዐሥራው ቅዱሳት መጻሕፍት/ማስረጃዎችን በዝርዝር እንመለከታለን...ይቀጥላል ክፍል ሁለት ይቀጥላል ምንጭ:-ተዋህዶ-ሀይማኖታችን blogs የሥላሴ በረከት በሁላችን ይደር አሜን
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
አስተያየቶች ለጥፍ (Atom)
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ