ቅዳሜ 18 ጁላይ 2015
ሰባቱ ሰማያት በእለተ እሁድ ከተፈጠሩ ፍጥረታት መካከከል ሰባቱ ሰማያት ዋነኛዎቹ ናቸው፡፡ በቅድሚያ ሰማይ ማለት ምን ማለት ነው? ሰማይ ማለት በዕብራይስጡ-- ሻማይም፡በሱርስት--ሼማያእ፡በዐረብ-- ሰማእ ማለት ሲሆን ፍቺውም በቁሙ ስፉህ(ሰፊ)ዝርግ ልዑል ምጡቅ ጠፈር ከራሳችን በላይ ርቆ መጥቆ የሚታይ የማየት ፍጻሜ ወሰን ድንበር ማለት ነው፡፡ ሰማይ ማለት ስዕለ-ማይ(የውሀ ስዕል ምስል)ማለት ነው፡፡ ሰማይ ሲጻፍ በእሳቱ ‹‹ሰ››ነው ለምን? ቢባል (ሀ፡ለ፡ሐ፡መ፡ሠ፡ረ፡ሰ)ስንል ‹ሰ› የምናገኛት ሰባተኛ ላይ ሲሆን በዚህም ሰባቱ ሰማትን ያጠይቀናል፡፡ ሰባቱ ሰማያትን እግዚአብሔር አምላክ የፈጠረው በኋላ የሚፈጥራቸው ፍጥረታት (መላእክትና ሰው) ይኖሩባቸው ዘንድ እንደ ጥሩ ወዳጅ የፈጠራቸው ናቸው፡፡ ጥሩ ወዳጅ እንግዳ ከመጥራቱ በፊት ቤቱን አኑሮ ምግቡን መጠጡን አሰናድቶ በፍቅር እንዲቀብለው፤ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔ ርም እንግዳ ፍጥረታት ሰውና መላዕክት ይኖሩበት ዘንድ ሰባቱ ሰማያትን ፈጥሯል፡፡ ሰባቱ ሰማያት ብሩህ ሰማይ በመባል ይታወቃል፡፤ብሩህ መባላቸውም ቀና ብለን ከምናየው ጠፈር(ሰማይ) የተለዩ መሆናቸውን ለማመልከት ነው፡፡ ዕዝ.ሱቱ4፥4‹‹የሰማይ ምጥቀቱ ሳይታይ ሰባቱ ሰማያት ሳይቆጠሩ….›› ሰባቱ ሰማያት አፈጣጠራቸው እግዚአብሔር ከእሳት ሙቀቱን ትቶ ብርሃኑን ወስዶ ፈጥሯቸዋል፡፡ የሰባቱ ሰማያት ዝርዝር ከላይ ወደታች በግእዝ በዕብራይስጥ ጽርሀ አርያም ዊሎን መንበረ መንግስት ርቂዕ ሰማይ ውዱድ ሻሓቅ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ዝቡል ኢዮር ምኦን ራማ ምኮን ኤረር ዐርቦት ፩.ጽርኀ አርያም ከሰማያት ሁሉ በላ ናት ከርሷ በላይ ሌላ ሰማይ የለም፡፡መጨረሻዋንም የሚአውቀው ፈጣሪዋ እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ ለመንበረ መንግስት እንደ ጠፈር ሆና ታገለግላለች፡፡አሰራሯም እንደ አረፍትና እንደ ግድግዳ ነው፡፡ ፫፻(318)ሊቃውንት በቅዳሴያቸው ላይ ‹‹መንበሩ በእሳት ክሉል ወማህደሩ በማይ ጥፉር ወዲበ ተድባበ ቤቱ ህንባበ ማይ ዘኢትከዐው--ዙፋኑ የተቀጸረ ማደሪያው በውሀ የተታታ(የተሰራ) ነው ቤቱም ዙሪያው የውሀ ሻኩራ የውሀ መርገፍ አለ›› ፪.መንበረ መንግስት በሌላ አጠራር መንበረ ብርሀን፣መንበረ ስብሐት፣መንበረ ጸባዖት ትባላለች፡፡ አሰራሯ እንደ ቤተ-መቅደስ ሲሆን ሥላሴ በፈቃዳቸው ለጻድቃን ፣ለሰማእታት፣ለመላእክት ልታይ ባለ ጊዜ የሚገለጹበት ነው፡፡ እግዚአብሄር አምላክ መንበረ መንግስትን ለእሳት ሙቀቱን ትቶ ብርሀኑን ወስዶ ፈጥሯታል ት.ኢሳ6፥1‹‹ንጉስ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚብሄር በረጅምናከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት የልብሱ ዘርፍ ቤተ- መቅደሱን ሞልቶታል›› ት.ህዝ1፥26‹‹የእግዚአብሄር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበር ባየሁትም ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ›› ፫ .ሰማይ ውዱድ ማለት የተወደደ ሰማይ ማለት ሲሆን በኪሩቤል ጀርባ ላይ የተዘረጋች ሆና ለመንበረ መንግስት እንደ አዳራሽ፣ወለል የሆነች ናት፡፡ ት.ህዝ1፥22‹‹ከእንስሶችም ራስ በላይ የሚያስፈራ በረዶ የሚመስል የጠፈር አምሳያ በራሳቸው ላይ ተዘርግቶ ነበር›› መዝ.ዳዊት17፥10 ‹‹ተጽዕነ ላዕለ ኪሩቤል ወሰረረ ፤ወሰረረ በክነፈ ነፋስ--በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ ለመብረር ተፋጠነ ፤በነፋስ ክንፍ በረረ›› ፬.ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ‹‹መንግስተ-ሰማያት›› የምንላት ይቺ ሰማይ አሠራሯ እንደ ቤተ-መቅደስ ነው፡፡ 12ት ደጆችና የተዋቡ ከሌላው የተለየ ብርሀን አላት፣አዕማዶቿ(ምሰሶቿ) ፣ክዳኗ፣መርገፏ ብርሀን ነው፡፡በሰባት የእሳት መጋረጃና የእሳት አጥር የታጠረች ናት በጉበኖቿ ላይ የ12ቱሐዋርያት ስም፣በመድረኩ የ12ቱ ነገደ እስራኤል ስም፣በምሰሶዋ የጻድቃን ሰማዕታት ስም ተጽፏል፡፡ራዕ.ዩሐ21፥10-15 ሌላው በውስጧ ቁመቷና ወርዷ እኩል የሆነች ከብርሀን የተሰራች ‹‹ታቦት ዘዶር›› አለች ምሳሌነቷም የእመቤታችን ነው፡፡ ራዕ.ዩሐ11፥19‹‹በሰማይ ያለው የእግዚአብሄር ቤተ-መቅደስ ተከፈተ የኪዳኑም ታቦት ታየ›› አባ ህርያቆስ /መጽ.ቅዳሴ ገጽ265‹‹ታቦት ዘዶር እንተ ይእቲ እግዝእትነ ማርያም- ይቺም ታቦትዘዶር እመቤታችን ማርያም ናት›› ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በመጽሀፈ አክሲማሮስ ላይ ‹‹ወውስቴታ ታቦት ዘዶር ዘያበርህ በጸዳለ ሥሉስ--በሥላሴ ጸዳል የሚያበራ ታቦት ዘዶር በውስጧ አለ›› እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በታቦር ዘዶር መመሰሏ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሄር ዘንድ ተልኮ እመቤታችን የአምላክ ታቦት (ማደሪያ)መሆኗን ‹‹መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል የልዑል ሓይል የጸልልሻል ካንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሄር ልጅ ይባላል ››ሉቃ.ወ1፥35 ራዕ.ዩሐ3፥12‹‹ከአምላክ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱ ኢየሩሳሌምን›› ፭.ኢዮር ፮.ራማ ፯.ኤረር እነዚህ ሶስት ሰማያት ዓለመ-መላእክት ሲሆኑ አፈጣጠራቸው እግዜር ከእሳት ሙቀቱን ትቶ ብርሀኑን ወስዶ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ከሰሜን እስከ ደቡብ ጎዝጉዞ ዘርግቶ አንጥፎ ሰርቷቸዋል፡፡ የእሳት መጋረጃና የእሳት ቅጥር የተቀጠሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰማያት ሲፈጠሩ ወደ ውጭ የሚያስወጣ ፣የሚያስወጣ (ክፍተት)የላቸውም፡፡ከሰማይ ውዱድ እስከ ጽርሀ አርያም ድረስ ርሱ ባወቀው ማህተም አትሞ ገጥሟቸዋል፡፡
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
ልጥፎች (Atom)