ሐሙስ 2 ጁላይ 2015
ከትላንቱ የቀጠለ ስለ ሥላሴ አንድነት እና ሶስትነት ከመፅሀፍ ቅዱስ ጥቅሶች ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም ነው፡፡ ለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ /ዐሥራው ቅዱሳት መጻሕፍት/ ማስረጃዎችን በዝርዝር እንመለከታለን፡፡ ምስጢረ ሥላሴ በብሉይ ኪዳን 1. እግዚአብሔርም አለ፡- «ሰውን በመልካችን እንደምሳሌአችን እንፍጠር» ዘፍ.1-26 እዚህ ላይ «እግዚአብሔርም አለ» ሲል አንድነቱ፣ «እንፍጠር» ሲል ከአንድ በላይ መሆኑን ግሱ /ቃሉ/ ያመለክታል፡፡ ሦስት መሆኑን ግን በዚህ ቃለ አልወሰነም፡፡ 2. እግዚአብሔር አምላክ አለ፡- «እነሆ አዳም መልካሙንና ክፉውን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ» ዘፍ.3-22 በማለት ባለቤቱን አንቀጽን አንድ፣ አሳቡን ዝርዝሩን የብዙ አድርጐ ይናገራል፡፡ «እግዚአብሔር አለ » ሲል አንድነቱን፣ «ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ» ሲል ደግሞ ከአንድ በላይ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በዚህ ቃል ግን ሦስትነቱን አልወሰነም፡፡ 3. እግዚአብሔርም አለ፡- «ኑ እንውረድ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው፡፡» ዘፍ.11.6-8፡፡ «እግዚአብሔር አለ» ብሎ አንድነቱ፣ «ኑ እንውረድ» ብሎ ደግሞ ከአንድ በላይ መሆኑን ያመለክታል፡፡ 4. «በቀትርም ጊዜ እግዚአብሔር ለአብርሃም ተገለጠለት አብርሃም ሦስት ሰዎችን በፊቱ ቆመው አየ» ዘፍ.18.1-15 በማለት እግዚአብሔር አንድ መሆኑንና ሦስት አካል ያለው መሆኑን ወስኖ ያስረዳናል፡፡ 5. «እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር ነኝ» ዘጸ.3-6 ሲል «አምላክ፣ አምላክ፣ አምላክ» ብሎ ሦስትነቱን፣ «እኔ እግዚአብሔር ነኝ» ብሎ ደግሞ አንድነቱን ገልጾ ተናግሯል፡፡ 6. «የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች፣ በእግዚአበሔርም ቃል ሰማዮች ጸኑ፣ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ» መዝ.32-6፡፡ 7. ነቢዩ ኢሳይያስም «ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በልዑል ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ አየሁት... ሱራፌልም ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያሉ ይጨሁ ነበር፡፡» ኢሳ.6.1-8 በማለት ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ብሎ ሦስትነቱን፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአበሔር ብሎ ደግሞ አንድነቱን አይቶ መስክሯል፡፡ ምስጢረ ሥላሴ በሐዲስ ኪዳን በአዲስ ኪዳንም የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት /ምስጢረ ሥላሴ/ በምስጢረ ሥጋዌ በሚገባ ታውቋል፡፡ ይኸውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ / ሰው ሆኖ/ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ፣ አብ በደመና ሆኖ «የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚላችሁን ስሙት» ሲል፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በራሱ ላይ በርግብ አምሳል ሲወድቅበት ታይቶአል፡፡ /ማቴ.3.16-17፣ ማር.1.9-11፣ ሉቃ.3.21-22፣ ሉቃ.1.32-34/ በዚህም እግዚአብሔር በአካል ሦስት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤልም እመቤታችንን ባበሠራት ጊዜ «መንፈስ ቅዱስ በአንች ላይ ይመጣለ፣ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንች የሚለደው ቅዱሱ የአግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡» ብሎ የሥላሴን ሦስትነት በግልጽ ተናግሯል፡፡ ሉቃ.1-35፡፡ እራሱ ባለቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የማዳን ሥራውን ፈጽሞ ከማረጉ በፊት ለደቀመዛሙርቱ ቋሚ ትዕዛዝ ሲሰጥ «እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ... ደቀመዛሙርት አድርጓቸው» ብሏል ማቴ.28.19-20፡፡ «ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፡፡» ብሏል ዮሐ.15.26፣ 14.16-17፣ 25-26፡፡ ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ የሥላሴን ሦስትነት ገልጾ ተናግሮአል፡፡ «የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔርም ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን» 2ኛ ቆሮ.13-14፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በጻፈው መልእክቱ «በሰማይ የሚመሰክሩ ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም አብ፣ ልጁም፣ መንፈስ ቅዱስም ናቸው፡፡ 1ኛ.ዮሐ.5-7፡፡ እነዚህ ሦስቱም አንድ ናቸው፡፡» በማለት የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት በግልጽ ያስረዳናል፡፡ /ይህንን ቃለ በ1886 ዓ.ም ከታተመው የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ እትም ይመልከቱ/፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የኪንግ ጀምስ የእንግሊዝኛውን መጽሐፍ ቅዱስ እትም ብንመለከት ይህነን አማናዊ የሥላሴን ምስጢር በትክክል ይመሰክራል/፡፡ ወንጌላዊው ቅድስ ዮሐንስም «በራእዩ እነሆም በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፣ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱም ስም የመንፈስ ቅዱስም ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ» ራእ.14-1፡፡ በማለት በገጸ-ልቡናቸው ስመ ወላዲ፣ ስመ ሠራፂ የተጻፈባቸውን የሥላሴን ልጆች አይቷል፡፡ በዚህም የሥላሴን ልዩ ሦስትነት በግልጽ መስክሯል፡፡ ከላይ በዝርዝር የተገለጹትና እነዚህን የመሳሰሉት ሁሉ እግዚአብሔር አንድነቱንና ሦስትነቱን የገለጸባቸው ምስክሮች ናቸው፡፡ የምስጢረ ሥላሴ ትምህርት/ምስክርነት በሊቃውንት ምስጢረ ሥላሴ በሊቃውንትም ትምህርት የአብ መላዲነት፣ የወልድ ተወላዲነትና የመንፈስ ቅዱስ ሠራፂነት ነው፡፡ አብ ተወላዲ አይባልም፣ ወልድ ወላዲ አይባልም፡፡ ወላዲ፣ ተወላዲ፣ ሠራፂ የሚባሉት ቃላት ሦስት አካላት ለየብቻ የሚታወቁባቸው የግብር ስሞች ናቸው፡፡ ሊቃውንት አባቶቻችን በሃይማኖተ አበው ምሳሌ ሲመስሉ ምሳሌ ሠይሐጽጽ /ጎደሎ ምሳሌ/ በማለት አንዳንድ ምሳሌዎችን ያቀርባሉ፡፡ ምሳሌውንም ጎደሎ የሚሉበት ምክንያት ለምስጢረ ሥላሴ ሙሉ በሙሉ ምሳሌ የሚሆን ሲያጡ ነው፡፡ ይህንንም የሥላሴን ሦስትነትና አንድነት ሐዋርያት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በተማሩት መሠረት በሚከተሉት ሦስት ምስሌዎች በሚገባ ገልጸውታል፡፡ የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በነፋስ፣ በፀሐይ፣ በአሳት ይመሰላል፡፡ 1. የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በሰው ምሳሌ ይገለጻል፡፡ ሰው በነፍሱ ሦስትነት አለውና ነው፡፡ የኸውም ልብነት፣ ቃልነት፣ ሕይወትነት ነው፡፡ ስለዚህ በሰው ነፍስ፡- በልብነቷ አብ፣ በቃልነቷ ወልድ፣ በሕይወትነቷ መንፈስ ቅዱስ ይመስላሉ፡፡ የነፍስ ልብነቷ፣ ቃልነቷን፣ ሕይወትነቷን ከራሷ ታስገኛለችና፡፡ ቃልና ሕይወት ከአንዷ ልብ ስለተገኙ በከዊን / በመሆን/ ልዩ እንደሆኑ በመናገርም ይለያሉ፡፡ እንዲሁም አብ ወልድን በቃል አምሳል ወለደው፣ መንፈስ ቅዱስንም በእስትንፋስ አንጻር አሰረጸው፡፡ ነፋስ ስትገኝ በሦስትነቷ በአንድ ጊዜ ተገኘች አንዷ ልብነቷ ቀድሞ ቃልነቷና እስትንፋስነቷ በኋላ አልተገኙም፡፡ ሰው በዚህ አኳኋን በነፍሱ የሚመስለው ስለሆነ እግዚአብሔር «ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር» ዘፍ.1-26 ብሎ ተናገረ፡፡ ስለዚህ ነፍስ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ / ሕይወት/ መሆን የከዊን /የመሆን/ ሦስትነትን ነገር በተናገረበት ድርሳን እንዲህ አለ፡፡ «አምላክ ውእቱ አብ፣ ወአምላክ ውእቱ ወልድ፣ በአምላክ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ወኢትበሀሉ ሠለስተ አማልእክተ አላ አሐዱ አምላክ ብሏል፡፡ ይህም ማለት አብ አምላክ ነው፣ ወልድም አምላክ ነው፣ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው ነገር ግን ሦስቱ አማልክት አይባሉም፣ አንድ አምላክ እንጂ፡፡» ማለት ነው፡፡ ሥላሴ በፀሐይ ይመሰላሉ፣ ፀሐይ አንድ ሲሆን ሦስትነት አለው፡፡ ይኼውም ክበቡ ብርሃኑ፣ ሙቀቱ ነው፡፡ ክበቡ አብ፣ ብርሃኑ ወልድ፣ ሙቀቱ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ፡፡ «አብ ፀሐይ፣ ወልድ ፀሐይ፣ መንፈስ ቅዱስ ፀሐይ አሐዱ ውእቱ ፀሐየ ጽድቅ ዘላዕለ ኩሉ» እንዳለ /ቅዱስ አባ ሕርያቆስ/፡፡ ሥላሴ በእሳት ይመሰላሉ፡፡ እሳት አንድ ሲሆን ሦስትነት አለው፡፡ ይኼውም አካሉ፣ ብርሃኑ፣ ዋዕዩ /ሙቀቱ/ ነው፡፡ በአካሉ አብ፣ በብርሃኑ ወልድ፣ በዋዕዩ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ፡፡ «አብ እሳት ወልድ እሳት ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ እሳተ ሕይወት ዘእምአርያም፡፡» እንዳለ /አባ ሕርያቆስ/ «አምላክህ እግዚአብሔር የሚባላ እሳት ቀናተኛም አምላክ ነው፡፡» ዘዲ. 4-24፡፡ ሥላሴ በፀሐይና በእሳት መመሰላቸውንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ለሐዋርያት «እኔና አባቴ መንፈስ ቅዱስም እሳትና ነበልባል ፍሕምም ነን» በማለት አስተምሮአቸዋል፡፡ ሐዋርያትም ይህንን ጽፈውት ቀሌመንጦስ በተባለው መጽሐፍ ይገኛል፡፡ / ቅዳሴ ሠለስቱ ምእትን/ ይመልከቱ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ አንድ ነፍስ፣ አንድ ፀሐይ፣ አንድ እሳት፣ እንጂ ሦስት ነፍስ፣ ሦስት እሳት፣ ሦስት ፀሐይ አይባሉም፡፡ ሥላሴም በአካል፣ በስም፣ በግብር ሦስት ቢባሉ በባሕርይ፣ በሕልውና፣ በፈቃድ፣ በመለኮት አንድ ናቸው አንጂ እማልክት አይባሉም፡፡ የቂሣርያው ሊጳጳስ ቅዱስ ባስልዮስ «እንዘ አሐዱ ሠለስቱ ወእንዘ ሠለስቱ አሐዱ ይሤለሱ በአካላት ወይትዋሐዱ በመለኮት» እንዳለ፡፡ ይህም ማለት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆኑ ሦስት ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸው፡፡ በአካል ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ናቸው፡፡ ማለት ነው፡፡ ይህም ሰው በሚረዳው መጠን ለመግለጽ ያህል ነው እንጂ ከፍጥረት ወገን ለሥላሴ የሚሆን በቂ ምሳሌ የለም፡፡ የተመሰለ ቢመስል ሕጸጽ /ጎደሎ/ ምሳሌ ነው፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር Source : http://eotc- mkidusan.org
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
አስተያየቶች ለጥፍ (Atom)
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ